Events

ለኤክስፖርት ስጋ ምርመራ ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቆ ተመረቁ

****የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን UNIDO ከተሰኘ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር ለኤክስፖርት ስጋ ምርመራ ባለሙያዎች በ ISO ስታንዳርድ ላይ በተከታታይ ዙሮች በቢሾፍቱ ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቆ ተመረቁ፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ የስጋ ምርቷን ወደ ውጭ በመላክ የተቀባይ አገራትን ስታንዳርድ ያሟላ እንዲሆን የሚደረገውን የቁጥጥር ስራ አቅም የሚያጠናክርና የተቀባይ አገራትን ቁጥር እንዲጨምር ለማስቻል ያለመ በመሆኑ ይህን ስልጠና አጠናቃችሁ ለዛሬዋ የምረቃ ዕለት በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ያሉት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ናቸው፡፡
አያይዘውም በቅርቡ አገራችን ኢትዮጵያ የስጋ ምርቷን ወደ ቻይና ለመላክ በዝግጅት ላይ በመሆኗ ለዚህ ትልቅ መደላድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡በመጨረሻም ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታችሁ ወቅት ያገኛችሁትን እውቀት በተግባር ላይ እንደምታውሉት እምነቴ የፀና ስለሆነ ለዛሬዋ የምረቃ ስነስርዓት በመብቃታችሁ በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ ለተመራቂዎቹ ሰርተፊኬት የመስጠት ስነስርዓት ተካሂዶ ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

ለእንስሳት ጤና ሐኪሞችና መለስተኛ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማሳጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

****

ከኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና ጣቢያዎች ለመጡ የእንስሳት ጤና ሐኪሞችና መለስተኛ ባለሙያዎች በደረጃ እድገት መሰላል መመሪያ ላይ በአዳማ ከተማ የግንዛቤ ማሳጨበጫ ስልጠና ተሰጠስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ሲሆኑ እሳቸውም ምንም እንኳን ይህ የደረጃ እድገት መሰላል መመሪያ በተለያዩ ምክንያቶች ለረጅም ጊዚያት ሳይፀድቅ በመቆየቱ በባለሙያዎቹ ላይ የስራ ተነሳሽነትን ሊቀንስ እንደሚችል ቢታመንም አሁን ግን በኢፌዴሪ ግብርና ሚ/ርና በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ቅንጅት ጭምር ተሰርቶና ፀድቆ በመምጣቱ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡አያይዘውም ይህ መመሪያ  አንዱ ከአንዱ ጋር የሚወዳደርበት ሳይሆን የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟሉ ባለሙያዎች ሁሉ ወደሚቀጥለው ደረጃ የሚያድጉበት በመሆኑ ተጠቃሚነታችሁና የስራ ተነሳሽነታችሁ እንደሚጨምር እምነታቸውን ገልፀው ይህን መመሪያ ለማስፈፀም ይቻል ዘንድ እናንተን የሚወክሉ የኮሚቴ አባላት ተመርጠው ወደ ስራ መግባታቸውን እና የዛሬው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩም በእነሱ የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል፡፡በመቀጠል ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በመጡ የአደረጃጀትና ምዘና አናሊስት ባለሙያዎች በአቶ ገረመው ቀናቴ እና በአቶ ተገኝ አንሙት ፀድቆ የመጣው የእንስሳት ጤና ሐኪሞችና መለስተኛ ባለሙያዎች የደረጃ እድገት መመሪያ ላይ ሰፊ ገለፃ ካደረጉ በኋላ ከተሳታፊዎች ለተነሱ የግልፅነት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡በመጨረሻም እያንዳንዱ ባለሙያ የደረጃ እድገት መሰላል ማመልከቻ ቅፁን እንዲሞላ የማድረግ ስራ ተሰርቷል፡፡

የኢፌድሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን መ/ቤት ተገኝተው የስራ ጉብኝት አደረጉ

****

የኢፌድሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ግርማ አመንቴ ከስራ አማካሪዎቻቸው ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን መ/ቤት በመገኘት የስራ ጉብኝት አደረጉ፡፡  በጉብኝቱ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ከማኔጅመንት አባሎቻቸው ጋር በመሆን የእንኳን ደሀና መጣችሁ አቀባበል አድርገው ክቡር ሚኒስቴሩ የስራ አማካሪዎቻቸውን ጭምር ይዘው ባለስልጣን መ/ቤቱ የተሰጠውን ትልቅ ሀገራዊ ተልእኮ ለመረዳትና አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ እዚህ ድረስ በመምጣት ላደረጉት የስራ ጉብኝት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም የባለስልጣኑን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው ደንብ ቁጥር 509/2014 መሰረት የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እንዲያስችለው በተቋሙ የተፈጠረውን መዋቅራዊ አደረጃጀት ምን እንደሚመስል እና የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ሲል ያጋጠሙትን ችግሮች፤ ችግሮችን ለመፍታት የተሄደበትን ርቀት በተመለከተ ገለፃ ቀርቦላቸዋል፡፡

አምባሳደር ድሪባ ኩማ አያይዘውም ባለስልጣን መ/ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አብራርተው ነገር ግን በሚኒስትሮች ም/ቤት በፀደቀው ደንብ ቁጥር 509/2014 መሰረት ከተሰጠው ተግባርና ኋላፊነት አኳያ እንዲሁም ተቋሙ እንደ አዲስ የተቋቋመ በመሆኑ ስራዎችን ለማከናወን የተለያዩ ችግሮች እንዳጋጠሟቸው አብራርተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የበጀት ዕጥረት፤ የተሸከርካሪ እጥረት፤ የራሱ የሆነ ቋሚ ቢሮ ያለመኖር፤ ከስራችን ጋር አግባብነት ያላቸው ረጂ ድርጅቶች ያለመምጣት ተጠቃሾች እንደሆኑና ለወደፊት እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው ዘመኑ የሚዋጀውን ጠንካራ የቁጥጥር ተቋም ለመፍጠር ሚኒስቴር መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊያግዘን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኢፌድሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ግርማ አመንቴ በስራ ጉብኝታቸው ሁሉንም የስራ ክፍሎች ተዟዙረው ከጎበኙ በኃላ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከተቋቋመ ጀምሮ እሰካሁን ድረስ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታና የሚደነቅ ነው በማለት መስሪያ ቤቱ ግዙፍ እና በግብርናው ዘርፍ በርካታ የቁጥጥር ስራዎችን የሚሰራና እየሰራ ያለ ተቋም በመሆኑ በተለይም አገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንድታገኝ ትልቅ ድርሻ ያለው በመሆኑ ይህንንም ለማሳካትና በታቀደው ልክ ለመሄድ ከሌሎች ተቋማት እና አጋር አካላት ጋር በቅንጅት  መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለዉም የተነሱ ችግሮች እንደ ክብደታቸውና አንገብጋቢነታቸው  በቅደም ተከተል እየታዩ መፍታት እንደሚገባ አብራርተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም የጀመረውን ድጋፍና እገዛ አጠናክሮ በመቀጠል ሀገራዊ ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የጸረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ 674/2002ን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሄደ፤

****

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በደንብ ቁጥር 509/2014 ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባራት መካከል የጸረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር ማካሄድ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ ያለውን የጸረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ 674/2002 ን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ላይ በአደማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ የጸረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ዋነኛ ዓላማ ፍቱንነቱና ጥራቱ ከፍተኛ የሆነ እና በሰው፣ በእንስሳትና በአካባቢ ላይ የሚያስከትለው ስጋት አነስተኛ የሆነ ጸረ ተባይ በመመዝገብ የገብያ ፍቃድ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደር ድሪባ አክለውም ባለፉት ጊዜያት ጠንካራ የጸረ ተባይ ምዝገባ እና ቁጥጥር ሥርዓት ባለመኖሩ ምክንያት በተለይም ወደ ውጭ በሚላኩ የሰብል ምርቶች ላይ ከጸረ-ተባይ ቅሪት መብዛት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ስጋት ፈጥሯል። በቀጣይም ተቀባይ አገራት ያላቸውን መስፈርቶች በማጥበቅ ላይ በመሆናቸው እና አሁን በሥራ ላይ ያለው የጸረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር አዋጅ 674/2002 ይኼን ለማስፈጸም ክፍተት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።

በአዋጅ 674/2002 ውስጥ በተግባር የታዩ ክፍተቶችን የሚሞሉና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያገናዘቡ ማሻሻያዎች በማድረግ የዘመነ አገራዊ የጸረ ተባይ አስተዳደርና ቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት ከባለሥልጣን መ/ቤቱ፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተውጣጡ ተመራማሪዎች፣ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት አምባሳደር ድሪባ የምክክር መድረኩም ዓላማ በተዘጋጀው ረቂቅ የማሻሽያ ሃሳብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ሃሳብና ግብዓት በማሰባሰብ ረቂቅ አዋጁን ማዳበር መሆኑን ገልጸዋል።

አዋጁን ለማሻሻል የተደረገውን ጥረት በባለሥልጣኑ የፀረተባይና ማዳበሪያ ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር በየነ ንጋቱ እንዲሁም የፀረ ተባይ ኢንስፔክተር ባለሙያ በሆኑት በአቶ ኃይሉ መካ የተሻሻለውን ረቂቅ አዋጅ  ቀርቦ በምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች አዋጁ ላይ የሠራተኞችን የሥራ ላይ ደህንነትና ጤንነት፣ የጸረ ተባይ ንግድንና አወጋገድን በተመለከተ ታሳቢ አድርጎ ሌሎች ቢጨመሩና ቢቀነሱ ያሏቸውን ኃሳቦች አንስተው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በተነሱ ኃሳቦች ላይ ማጠቃልያ የሰጡት በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሰሉ ዋጋው የማሻሻያ አዋጁ በረቂቅ ደረጃ ያለ በመሆኑ በምክክር መድረኩ የተነሱ ኃሳቦችን ታሳቢ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

አቶ መሰሉ አክለውም በጸረ ተባይ ምዝገባና ቁጥጥር ውጤታማ ሥራ ለመስራት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አውስተው ባለሥልጣን መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ተቀራርቦ መሥራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው የምክክር መድረኩ ተጠናቋል።

Food safety and Quality Management Practice practical training is happening now at Bishoftu Meareg Export Abattoir

Date: August 21, 2023
Bishoftu, Ethiopia
****
Ethiopian Agricultural Authority (EAA) with its development partner United Nations Industrial Development Organization (UNIDO) has organized and is providing hands-on practical training to 25 meat inspectors and experts coming from 11 Export abattoirs, 4 local abattoirs, EAA, and Halal Certification Department of Oromia Region Islamic Affair at Mearege Export abattoir Bishoftu, Ethiopia.

The training is supported by the UNIDO project “Capacity building to upgrade the livestock value chain in Ethiopia” financially supported by the Government of China under the Global Development and South-South Cooperation Fund.

The main objective of EAA is to establish and implement a strong regulatory system in the livestock sector to improve international and national competitiveness. EAA Director of Export Abattoir Inspection and Certification Directorate, Dr. Ayalew Shumet, officially opens the training. In the opening remark, He emphasizes the importance of building the capacity of experts working in the abattoir mandated for food safety and quality along the meat value chain and to achieve the objective of the authority. He notes that it is currently a main requirement for importing countries that meat inspectors acquire skills and knowledge and become certified in food safety and quality management practices based on international standards and practices.

Dr. Sentayhu Menda; UNIDO National Project Coordinator, stated in his keynote address that one of the project’s goal is to boost Ethiopian meat competitiveness in the global market by strengthening local institutions and human capacities. The project is working closely with the government to capitalize on its livestock resources.

The training will run for 12 days, from August 21 to September 1, 2023, and will be conducted by qualified INDIGO trainers.

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አመራሮችና ሠራተኞች የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽንን ጎበኙ

****

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አመራሮችና ሠራተኞች “ከቤተ ሙከራ እስከ አዝመራ" በሚል መሪ ሀሳብ ለሕዝብ ይፋ ሆኖ በሳይንስ ሙዚየም የተከፈተውን የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ጎብኝተዋል፡፡

ግብርና የአገሪቱ የጀርባ አጥንት መሆኑንና ከእጅ ወደ አፍ የነበረው የግብርና ስራ በአሁን ወቅት ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኑነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አዲስ እጅጉ የጉብኝቱ ዋና አላማም አመራሩና ሠራተኛው ግብርናው ከነበረበት ኋላ-ቀር አሰራር ወጥቶ አሁን የደረሰበትን ደረጃ አውቆ ለበለጠ ውጤት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር አዘጋጅነት "ከቤተ ሙከራ እስከ አዝመራ" በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም ይፋ የሆነው የግብርና ሳይንስ ኤግዚቢሽን ከሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መከፈቱ ይታወሳል።

ለበለጠ መረጃ፦

ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et

ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/Ethiopian Agricultural Authority

ቴሌግራም፡- eaa_123

 

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤

ምክር ቤቱ የዕፅዋት ዘርን ለመደንገግ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፤

****

የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ17ኛ በመደበኛ ጉባዔው፤ የዕፅዋት ዘርን ለመደንገግ የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ፤ ረቂቅ አዋጁ የዕፅዋት ዝርያን በማዘመን ቴክኖሎጂ እና ኢንቨስትመንትን በመሳብ በዓለም አቀፍ ገበያው ተወዳደሪ እና ተሳታፊ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩ ምርቶችን በማሳደግ እና የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ሰብሳቢው አክለው አብራርተዋል፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎችና ከሚመለከታቻው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግ ለረቂቅ አዋጁ የሚሆኑ ግብአቶችን መሰብሰብ እንደተቻለ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ ለምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፤ ለአርሶ አደሩ ጥራቱን የተበቀ ምርጥ ዘር በአይነት እና በመጠን በማቅረብ ለሀገር ዕድገት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ሀገር ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ወጪን የሚቀንስ በመሆኑ ረቂቅ አዋጁ ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ዘርፈ-ብዙ ጥቅም እንዳለው የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1288/2015 አድረጎ በምሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

©የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግብርና እና ሳይንስ አውደ ርዕይን መርቀው ከፈቱ

****

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በግብርና ሚኒስቴር የተዘጋጀውን የግብርና እና ሳይንስ አውደ ርዕይን በሳይንስ ሙዚየም መርቀው ከፍተዋል።

አውደ ርዕዩ የምርታማነት ቴክኖሎጂ ፣ የምርምርና ፈጠራ ስራዎች ፣ ዲጂታላይዜሽን ግብርና እና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮረ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ የሚቀርብበት ነው።

በግብርና ሚኒስቴር ፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት ''ከቤተ ሙከራ ወደ አዝመራ '' በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ የጀመረው አውደ ርዕዩ 70 የውጭና የሀገር ውስጥ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ምርቶቻቸውን እና የግብርና ቴክኖሎጂዎቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም፣ አውደ ርዕዩ በፓናል ውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች የግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የስራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም ሌሎች የግብርና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይካሄዳል።

በአውደ ርዕዩ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ፣ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች ተገኝተዋል።

 

«በእንስሳት ኳራንቲን ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ከባለድርሻ አካላትን ጋር ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር ሊኖር ይገባል!»

****

ዶ/ር ራሻድ ሙሀመድ በባለሥልጣኑ የድሬደዋ የእንስሳት ኳራንታይን ጣቢያ አስተባበሪ
****

የእንስሳት ኳራንታይን አሰራር ዓለምአቀፍ የሕግ ማዕቀፍን ተከትሎ የሚከናወን ቢሆንም አገራችን ኢትዮጵያ የእንስሳት ኳራንታይንን አስመልክቶ ዓለምአቀፉን አሰራር ለማሟላት ባለመቻሏ ባላት የእንስሳት ኃብት ልክ በዓለም አቀፉ ገበያ ተወዳድራ ገብያውን ሰብራ መግባትና ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡ ይሁንና የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግስት የእንስሳት ኳራንታይን ሥራ በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ እንዲሰራ ለማድረግ የፌዴራል መንግስት የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 45 ንኡስ አንቀጽ 1 መሠረት “የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን”ን አቋቁሟል፡፡

የባለስልጣኑን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው ደንብ ቁጥር 509/2014 መሠረትም ባለሥልጣኑ የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያዎችና ቼክ ፖስቶችን በመገንባትና በግንባታ ላይ ያሉትን ደረጃቸውን እንዲጠብቁና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የውስጥ አደረጃጀታቸውን በመፈተሸ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ሙያዊ ድጋፍና ቁጥጥር በማድረግ በሌሎች አገራት ተቀባይነት እንዲኖራቸው እንዲሁም በተቀባይ ሀገሮች በማስገምገም እውቅና እንዲያገኙ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ክፍልም የእንስሳት ኳራንታይን ጣቢያዎች አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የሚለውን የድሬደዋ የእንስሳት ኳራንታይን ጣቢያን እንደናሙና በመውሰድ ከኳራንቲን ጣቢያው አስተባበሪ ዶ/ር ራሻድ ሙሀመድ ጋር አጭር ቆይታ በማድረግ እንደሚከተለው የሚያስቃኛችሁ ይሆናል፤ መልካም ቆይታ!

ሕዝብ ግንኙነት፦ በድሬደዋ የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ራሻድ፦ የድሬዳዋ የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያ ከተቋቋመበት ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ኳራንቲን ጣቢያው ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዋነኛነት የቁም እንስሳትን ወደ መካከለኛው ምስራቅና አረብ አገሮች እንዲሁም አጎራባች የአፍሪካ አገሮች ማለትም ጅቡቲ፣ ሶማሌላንድ፣ ሊቢያ፣ ግብፅ የመሳሰሉት አገሮች ላይ ኤክስፖርት ያደርጋል፡፡ በተጨማሪም የእንስሳት ተረፈ ምርቶችን እንደ ማርና ወተት የመሳሰሉትን ወደ ውጪ የመላክ ሥራ የሚሰራ ሲሆን በዚህም በዓመት ከ20 እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ከ2013 ጀምሮ በኮቪድና ሌሎች ምክንያቶች የኤክስፖርት መጠኑ እየቀነሰ የመጣበት ሆኔታ አለ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ኳራንቲን ጣቢያው በተሰጠው ወሰን ውስጥ ወደ ውጭ የሚላኩ የቁም እንስሳት በኳራንቲን የቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ከማድረግ አኳያ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ራሻድ ፦ የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያው እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን ኤክስፖርት ሲያደረግ የሌሎች አገሮችን ፍላጎትንና የኳራንቲን ጣቢያው ሕግና መመሪያ መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ወደ አገር ውስጥም ሲገባም በተመሳሳይ በተቀመጠው ሕግና መመሪያ መሰረት እየተከናወነ ነው የሚገባው፡፡ በሁሉም አገሮች ላይ የተለያዩ የእንስሳት በሽታዎች ስለሚገኙ እነዚህም በሽታዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር እንዳይዛመቱ የእንስሳት ኳራንቲው ጣቢያው ጥብቅ ምርመራና ፍተሻ ያደረጋል፡፡ በዚህም ወደ ውጭ የሚላኩ እንስሳት በኳራንቲን የቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉና በዓለም አቀፍ ገበያው ተወዳዳሪ በመሆን አገራችን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወንን እንገኛለን፤ ይህ ግን በቂ አይደለም፡፡ በዘርፉ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መኖር ወሳኝነት አለው፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድን ጨምሮ ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላችሁ ቅንጅታዊ አሰራር ምን ይመስላል?

ዶ/ር ራሻድ፦ ሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ የዘርፉ ዋነኛ ፈተና ነው፤ በተለይ እንደ እኛ አካባቢ ከ2010 ጀምሮ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በሁሉም ክልል የሚገኙ ከእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያ ባለሙያዎች ጋር ተጣምሮና እስከ ታች ድረስ ወርዶ በቅንጅት ባለመስራቱ የችግሩ መጠን እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ክልሉም ለጣቢያችን ሲያደርግ የነበረው ድጋፍ እንብዛም ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ በአገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰው ያለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል በፌደራል ደረጃ በክቡር ጠ/ሚኒስቴሩ፣ በክልል ደረጃ በክቡራን ርዕሰ መስተዳደሮች የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ውጤት መታየትም ጀምሯል፡፡ ይህ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ ነገር ግን በኮሚቴ ብቻ ሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድን መቆጣጠር ስለማይቻል መላ ህብረተሰቡ በተለይም የአካባቢያችን ማህበረሰብ ከኮሚቴውም ሆነ ከጣቢያችን ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ህገወጥነትን ልንከላከል ይገባል።

ሕዝብ ግንኙነት፦ በኳራንቲን ጣቢያው የሚሰጡ አገልግሎቶች ከብልሹ አሰራርና ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ፣ ቀልጣፋና የተገልጋዩን እርካታ በሚያሳድግ መልኩ እንዲሆን የሚከናወኑ ተግባራትን ቢገልጹልን?

ዶ/ር ራሻድ ፦ በእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች የስራ ባህሪው ከብዙ ባለሀብቶች ጋር የሚያገናኛቸው በመሆኑ እና ሥራዎች በሕግ ማዕቀፍ የታገዙ ባለመሆናቸው ባለሙያዎችን ለኪራይ ሰብሳቢነት እና ለመልካም አስተዳደር የተጋለጡ ያድርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም በአጠቃላይ በኳራንቲን ጣቢያዎች የሚታየውን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባርን ለመቀነስ የሚቻለው ባለሥልጣን መ/ቤቱ የአሰራር መመሪያዎችንና ማኑዋሎችን አዘጋጅቶ ወደ ታች በማውረድ እና ጥብቅ ክትትል በማድረግ የኳራንቲን አገልግሎት አሰጣጡ ለሁሉም ተገልጋዮች በእኩል ደረጃ የሚሰጥበትን ሁኔታ መፍጠር ሲቻል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?

ዶ/ር ራሻድ፦ ማስተላለፍ የምፈልገው እስከአሁን በግብርና ሚ/ር ሥር ስለነበርንና ለእንስሳት ልማቱ እንጅ ለቁጥጥሩ በቂ ትኩረት ስለማይሰጠው የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያዎች ከድጋፍና ክትትል፣ ከበጀትና ከትራንስፖርት አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች የነበሩባቸው በመሆኑ በአዲሱ አደረጃጀት ባለሥልጣን መ/ቤቱ እነዚህ ችግሮች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ትኩረት መስጠት አለበት እላለሁ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

ዶ/ር ራሽድ፦ እኔም አመሰግናለሁ!

ለበለጠ መረጃ፦

ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et

ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/Ethiopian Agricultural Authority

ቴሌግራም፡- eaa_123

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤

 

በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የላቦራቶሪ ጥራት ፍተሻ አገልግሎት አሰጣጥ ዓለምአቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸወሰ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፤

****

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ተገኝቶ የሥራ ክፍሎችን የሥራ እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ ያደረገ ሲሆን የባለስልጣን መ/ቤቱን የ2015 በጀት ዓመት የ 9 ወራት እቅድ አፈፃፀም በተመለከተ ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮችና ዳይሬክቶሬቶች ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡

በዚህም የእንስሳትም ሆነ የእፅዋት ምርቶች እንዳይበከሉ ጥራቱን የጠበቀ የላብራቶሪ ፍተሻ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው በተለይም ከውጭ የሚገቡ የዘር ዓይነቶች ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ብሎም የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የተቋሙ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዘርፉ ብቁ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ አስገንዝቧል።

የወንዝ ዳር የግብርና ምርት ቁጥጥርን በሚመለከት በአመጋገብ ችግር ከሚመጡ በሽታዎች የዜጎችን ጤና ከመታደግ አኳያ ተቋሙ መከታ ሊሆን እንደሚገባ የተናገሩት የቋሚ ኮሚቴው የመስክ ቡድን አስተባባሪ የተከበሩ አቶ ባርጠማ ፍቃዱ ተቋሙ የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግብ በዘርፉ የተጀመሩት የሪፎርም ስራዎች ተጠናቀው ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በሂደት ላይ ያሉ የሕግ ማዕቀፎች ወደ ስራ እንዲገቡ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት የተከበሩ አቶ ባርጠማ የእንስሳት እና የእፅዋት ዘር አስመጪዎች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በማጠናከር ሕገ-ወጥነትን መከላከል ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ተቋሙ ዓለምአቀፍ ተፎካካሪ መሆን መቻል እንዳለበት ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው አስተባባሪ ተቋሙ ባስቀመጠው ስታንዳርድ የማይሰሩ ድርጅቶች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድና የባለሙያዎችን አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በሁሉም ላብራቶሪዎች የሚሰጡ አገልግሎቶች በዓለምአቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸውና ተአማኒ የቁጥጥር ተቋም እንዲሆን የተጀመሩ ሥራዎችን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ነገር ግን በተቋሙ ጥርት ያለ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደር ድሪባ አያይዘውም የማያሰሩ የፖሊሲ ማዕቀፍ እና ደንቦች ሊሻሻሉ እንደሚገባቸው ጠቁመው ለዚህም የቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ከአመራሮቹና ሠራተኞቹ ጋር ወይይት አካሄደ፤

****

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን “ድሎችን የማጽናት ፈተናዎችን የመሻገር!” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከባለሥልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞች ጋር በባለስልጣኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ወይይት አካሄዷል፡፡

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ በውይይቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር አሁን ላይ አገራችን ባለፉት 5 ዓመታት በርካታ ታሪክ ቀያሪ የሆኑ ለውጦች ያስመዘገበች ቢሆንም የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነትና መሰል ችግሮች አሁንም ድረስ ፈተናዋ ሆነው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ሰላምን በማደፍረስ ሕዝብን ለማሸበርና አገር ለማፍረስ የሚደረጉ የተሳሳቱ አካሄዶች መኖራቸውን የገለጹት አምባሳደር ድሪባ ችግሮቹ ሕግን በተከተለ መንገድ በሰከነ መልኩ በውይይትና በሰላም እንዲፈቱ ሁሉም የዜግነት ድርሻቸውን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ድሎችን በማጎልበት፣ ፈተናዎች ላይ ደግሞ ተናቦና ተባብሮ በመስራት በአንድነት ለመሻገር የሁሉም አገር ወዳድ ሚና ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ሰላምን በማስፈን የአገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ፣ የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ በሚደረገው አገራዊ ጥረት የባለሥልጣን መ/ቤቱ ሠራተኞችና አመራሮች ድርሻውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ባለፉት 5 የለውጥ አመታት የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚመለከት “ድሎችን የማጽናት ፈተናዎችን የመሻገር!” በሚል ርዕስ ዝርዝር አገራዊ የውይይት ሰነድ በባለሥልጣኑ የእንስሳት ሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀሚድ ጀማል ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረበው ሰነድ ላይ ከሰላም፣ ከኑሮ ውድነትና ከተገኙ አገራዊ ስኬቶች ጋር በተያያዘ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡ በተለይም ከጎጠኝነትና ዘረኝነት አስተሳሰብ ወጥተን ሁላችንም ለሰላም ዋጋ በመስጠት በየተሰማራንበት የስራ መስክ ኃላፊነታችንን መወጣት አለብን፤ የኑሮ ውድነቱ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ለመንግስት ሰራተኛ በመንግስት በኩል ምን ታስቧል? አገልግሎት አሰጣጣችን ከሙስናና ከሕገ-ወጥ ተግባራት የጸዳ እንዲሆን በቀጣይ ሊታዩ ይገባሉ ያሏቸውንና ሌሎች በ5 አመቱ ውስጥ በተገኙ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

የመንግስት አቅጣጫዎች በየጊዜው እየቀረቡ ከሰራተኛው ጋር ውይይት እየተደረገባቸው የጋራ ኃሳብና አረዳድ እየያዝን ከሄድን ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ እድል ይሰጣል ያሉት በባለሥልጣኑ የእጽዋት ሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንዳለ ሀብታሙ የተጣለብንን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣትና የአገራችንን አንድነትና እድገት ለማረጋገጥ የባለሥልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞች ከአፍራሽ ድርጊቶች በመቆጠብ የተሰጠንን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ወንዳለ አክለውም የለውጡ መንግስት ለውጡን የጀመረው በሪፎርም በመሆኑና ሪፎርም ደግሞ በባህሪው በአጭር ጊዜ ሥር-ነቀል ለውጥ የሚያመጣና የሚተገበር ሳይሆን ረጅም ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ በአጭር ጌዜ የሕዝብን ፈላጎት ማሟላት እንደማይቻል በመገንዘብ ሁላችንም ከጽንፈኝነት፣ ከአክራሪ ብሔርተኝነት እና ከጎጠኝነት አስተሳሰብ ወጥተን ሪፎርሙን በመደገፍ አውንታዊ ሚናችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ተቋማችን የሬጉላቶሪ ተቋም መሆኑን በውል በመረዳት ከሌብነትና ከሕገ-ወጥ አሰራር የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት አቶ ወንዳለ ከተሰጠን ተግባርና ኃላፊነት ጎን ለጎን የአገራችንን ሰላም ከውጭና የውስጥ አፍራሽ ኃይሎች ልንጠብቅ ይገባል በሚል አሳስበው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

ለበለጠ መረጃ፦

ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et

ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/Ethiopian Agricultural Authority

ቴሌግራም፡- eaa_123

 

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤

የዘር ጥራት ቁጥጥር ሥርዓቱን በአገርአቀፍ ደረጃ ወጥና ተመጣጣኝ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለፀ፤ ****

12ኛው አገር አቀፍ የዘር ጥራት ቁጥጥር የጋራ የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ ከመጋቢት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተካሂዷል።

የመድረኩ ዋና አላማ ክልሎች ከፌዴራል ጋር በትብብር እንዲሰሩ እና መረጃ በቀላሉ በመለዋወጥ የዘር ቁጥጥር ሥራው ስኬታማ እንዲሆን ማስቻል መሆኑ የተናገሩት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ የዘር ጥራት ቁጥጥር ሥርዓቱን በአገርአቀፍ ደረጃ ወጥና ተመጣጣኝ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የዘር ጥራት ፍተሻ አሰራር በመስክና በላብራቶሪ ተቀራራቢነት እንዲኖረው መደረጉንም የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ መስፈርቱን የሚያሟላ ማንኛውም ዘር በቀላሉ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላኛው ማሰራጨት መቻሉንም ተናግረዋል።

የጥራት ቁጥጥር ተግባር ቅንጅታዊ አሰራርን የሚጠይቅ መሆኑንም የገለፁት አምባሳደሩ ተናቦ የመስራት ሁኔታው በይበልጥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውም አምባሳደር ድሪባ አሳስበዋል።

በደብብ ክልል የግብርና ግበዓት ቁጥጥርና ኳረንቲን ዋና ዳይሬክተር አቶ እዮብ ዋቴ ከድህነት ለመውጣት ጥራት ያለው ዘር ወደ አርሶ አደሩ በማድረስ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚቻለው ጥራት ያለውን ዘር ወደ አርሶአደሩ በማድረስ ነው ያሉት አቶ እዮብ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ ያለው የጥራት ቁጥጥር ተግባር እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሲዳማ ክልል የግብርና ግበዓት ቁጥጥርና ኳረንታዪን ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሰለሞን በበኩላቸው የአርሶ አደሩ ማሳ ላይ የዘር ጥራት ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሕገ-ወጥ የዘር ዝውውር እንዳይኖር ቁጥጥር እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ ጥራቱ የተረጋገጠ ዘር ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስጣን የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልሎች የግብርና ግበዓት ቁጥጥርና ኳረንቲን ዋና ዳይሬክተሮች እና የሚመለከታቸው አካላት በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተዋል።

@የደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ

«የመኖ ጥራትና ደኅንነትን በመጠበቅ የእንሰሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው!»

አቶ ዘላለም አበበ የእንስሳት መኖ ጥራት ደረጃ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር
****
የእንስሳት መኖ ጥራትና ደኅንነትን ማስጠበቅ ከእንስሳት ዘርፉ የሚገኜውን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እኛም በአገር አቀፍ ደረጃ የመኖ ምርት ጥራትና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ ምን እየተሰራ ነው ስንል ከግብርና ባለስልጣን የእንስሳት መኖ ጥራት ደረጃ ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከአቶ ዘላለም አበበ ጋር ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሕ/ግ፦ የስራ ክፍሉ በመኖ ላይ ሚኖረው የቁጥጥር ስልጣን እሰከምን ድረስ ነው?

አቶ ዘላለም ፦ በቀድሞው የእንስሳት መድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን በአዋጅ ቁጥር 728/2004 መሠረት፡- “መኖ ማለት ለንግድ ዓላማ የተመረተ ወይም የተዘጋጀ የእንስሳት ምግብ ነው” ሲል፤ በመመሪያ ቁጥር 16/2010 መሠረት ደግሞ መኖ ማለት በመኖ አምራች ድርጅት በሀገር ውስጥ የሚመረት፣ ከውጭ ወደ ሀገር የሚገባ፣ በሀገር ውስጥም ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ለንግድ የሚዘዋወር ወይም ወደ ውጭ ሀገር ገበያ ለሽያጭ የሚወጣ የእንስሳት ምግብ ነው ሲል ያስቀምጣል፡፡ በአዲሱ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በመኖ ላይ የሚኖረዉ የቁጥጥር ሥልጣን ደግሞ በንግድ መኖ (Commercial Feed) ላይ ብቻ ሲሆን፣ ቁጥጥር የሚያደርገውም በመኖ ጥራትና ደህንነት ላይ ብቻ ሲሆን የስራ ክፍሉም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመኖ ምርት ጥራትና ደህንነት ላይ ያስቀመጠውን ደረጃ መሰረት በማድረግ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡

ሕ/ግ፦ የመኖ ምርት ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የስራ ክፍሉ የሚያከናወናቸው ተግባራት ምን ምን ናቸው?

አቶ ዘላለም፦ የስራ ክፍሉ የመኖ ምርት ጥራትና ደህንነት ለማሰጠበቅ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል፦ የእንስሳት መኖ ግብዓትና ምርት ጥራትና ደህንት ባለስልጣኑ ባወጣው መስፈርት መሰረት በመገምገም ይመዘግባል፣ ለገበያ አንዲቀርብ ፈቃድ ይሰጣል፣ ያግዳል፤ ይሰርዛል ፣ አጠቃላይ የመኖ ደህንነትና ጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን ያቅዳል፣ አፈፃፀማቸውን በመገምገም ይተግብራል ፣ የእንስሳት መኖ ጥራትና ደህንነትን ለማረጋገጥ የቅድመና ድህረ ግብይት ናሙና ይሰበስባል፤ በላቦራቶሪ ምርመራ እንዲካሄድ ያደርጋል፣ ውጤቱንም መሰረት አድርጎ አግባብ ያለው እርምጃ ይወስዳል፣ ለእንሰሳት መኖ ባለሙያዎች እና ለእንሰሳት መኖ አስተዋዋቂዎች የሙያ ፈቃድ እንዲሰጥ እና እንዲታደስ ይከታተላል፣ ይገመግማል፣ ይፈፅማል፣ ከመኖ እና መኖ ጥሬ ዕቃ ጥራትና ጤንነት ጋር ተያያዥ የሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ያደርጋል ፣ ጥራትና ደኅንነቱ የተጠበቀ መኖ አቅርቦትን ለማረጋገጥ የጥራትና ደኅንነት ደረጃዎችን ያዘጋጃል፤ ሲፀድቅም ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፤ በተቀረጸው የሕግ ማዕቀፍ እና በፀደቀው ደረጃ መሰረት መከናወኑን መከታተልና ለአፈጻጸሙም አሰፈላጊውን ድጋፍና ቁጥጥር ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ሕ/ግ፦ ከ2006 ዓ.ም እስካሁን ድረስ በመኖ ደህነትና ጥራት አጠባበቅ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ቢጠቀሱ?

አቶ ዘላለም፦ የመኖ ጥራትና ደኅነትና ለማስጠበቅ ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ የንግድ መኖ አምራች ፋብሪካዎች፣ የመኖ ግብዓት አስመጪዎች እና የመኖና የመኖ ጥሬ እቃ ጅምላ ንግድ ድርጅቶች የተመዘገቡ ሲሆን በተጨማሪም ከባለሥልጣኑ መቋቋም በኋላ ለአምራቾችና ለተጠቃሚዎች በተከታታይ በተሰጠው ሥልጠና የመኖ ንግድ ሥራው እየተለመደ በመምጣቱ የማምረቻ ፋብሪካዎች በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ የሚገኝ የንግድ መኖ በመጠንም ሆነ በጥራት ብዙ ችግር ያለበት ሲሆን የጥራትና ደህንነት ቁጥጥሩ ካለፉት 8 ዓመታት ወዲህ በተሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችና የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎች በ2006 ዓ.ም ተመዝግቦ ከነበረውና አሁን ላይ ከ50% በላይ እድገት አሳይተዋል፡፡

ሕ/ግ፦ የመኖ ጥራትና ደኅንነት የቁጥጥር ስራ ለመስራት እንቅፋት የሆነው ችግር ምንድን ነው?
አቶ ዘላለም፦ የመኖ ጥራትና ደኅንነት የቁጥጥር ስራ ለመስራት እንቅፋት ከሆኑት መካከል አንዱ የመኖ ጥሬ እቃ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች መበራከት ሲሆን፣ የመኖ ጥሬ ዕቃዎችን ጥራትና ደህንነቱ በማይጠበቅበት ቦታ በማከማቸት እና ለመኖ አቀነባባሪዎች ዋጋ ጨምሮ ማቅረብ ነው፡፡ ሌላኛው ችግር ደግሞ የመኖ አምራች ድርጅቶች የራሳቸው የጥራት ምርመራ የላብራቶሪ ማእከል ስለሌላቸው፣ መኖ ለማምረት የሚጠቀሟቸውን የመኖ ጥሬ እቃ ሲቀበሉና በመጨረሻም ምርቱን አቀናብረው ለገበያ ሲያቀርቡ ምርቱ የተቀመጠውን የጥራትና ደኅንነት ደረጃ ማሟላቱን ለማረጋገጥ አዳጋች መሆኑ ነው፡፡

ሕ/ግ፦ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያላችሁ ቅንጅታዊ አሰራር ምን ይመስላል?

አቶ ዘላለም ፦ የመኖ ምርት ጥራትና ደህንነትን የማስጠበቅ ስራ በስራ ክፍሉ ብቻ ውጤታማ ማድረግ ሰለማይቻል ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦና ተቀናጅቶ መስራት ግድ ይላል፡፡ ስለሆነም ከጥናትና ምርምር ተቋማት፣ የመኖን ጥራትና ደህንነት ቁጥጥርን ከሚደግፉ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመወያት ፣ በመተባበርና በመቀናጀት እየሰራን እንገኛለን፡፡

ሕ/ግ፦ በመጨረሻም የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

አቶ ዘላለም፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የመኖ ጥራትና ደህንነት የቁጥጥር ስራን ውጤታማ ለማድረግ ራሱን በቴክኖሎጅ ማብቃት፣ ለቁጥጥር ስራ ምቹ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋትና ከተለመደው አሰራር ወጥቶ በላብራቶሪ ፍተሻ ላይ መሰረት ያደረገ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጂታዊ አሰራር በመፍጠር የተጠናከረ የቁጥጥር ስራ መሥራት አለበት፡፡ የግብርና ሚኒስቴርም ለመኖ ጥራትና ደህንነት መሰረታዊ ነገር የሆነውን የግብርና መልካም አመራረት (Good Agricultural Practices - GAP) ዘዴ እንዲስፋፋ ተግባሩን በበላይነት መምራት አለበት ስል መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

ለበለጠ መረጃ፦

ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et

ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/Ethiopian Agricultural Authority

ቴሌግራም፡- eaa_123

 

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤

“አስፈላጊ የሆኑ የእንስሳት መድኃኒቶች መዝርዝር መዘጋጀት የጸረ-ተሕዋሲያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ችግርን ለመቅረፍ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው!” ዶ/ር ሰለሞን ከበደ በባለሥልጣኑ የእንስሳት መድኃኒት ጥራትና ደረጃ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር

 

የጸረ-ተሕዋሲያን መድኃኒት የረቂቅ ነብሳት(ጀርሞችን) በመግደል ወይም እድገታቸውን በመግታት እንስሳትን፣ ሰዎችን እና እጽዋትን ከበሽታ እንዲድኑ የሚያደርግ መድኃኒት ሲሆን እ.ኤ.አ ከ 1940 ዓ.ም ጀምሮ የብዙ ሰዎችን እና እንሰሳትን ሕይወት ከበሽታ ሲታደግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን መድኃኒቶቹን በአግባቡ ለእንሰሳትም ሆነ ለሰው ጥቅም ላይ እንዲውል ባለማድረጋችን የጸረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ(Antibiotic resistance) እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ በፊት በሽታን ሲያድን የነበረ መድኃኒት አሁን ረቂቅ ነብሳትን ወይም ጀርሞችን መግደል ወይም እድገታቸውን መግታት አቅቶት በሽታን ማደን ሳይችል ሲቀር የጸረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ(Antibiotic resistance) ይባላል፡፡ የዓለም ባንክ ሪፖርት ቁልፍ ግኝቶች እ.ኤ.አ በ2017-2050 የዓለም ኢኮኖሚ ትንበያ ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ በጸረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ምክንያት እ.ኤ.አ. በ2050 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርታቸው(GDP) ኪሳራ ከ5 በመቶ በላይ እንደሚሆን፣ ተጨማሪ 28.3 ሚሊዮን ሰዎች ለከፍተኛ ድህነት እንደሚዳርግ፣ የኤክስፖርት መጠን በ3.8% እንደሚቀንስ፣ የጤና እንክብካቤ ወጪዎች ከ300 ቢሊዮን ዶላር እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር በዓመት እንደሚያስወጣ እና የእንስሳት ምርት በ11%  እንዲያሽቆለቁል እንደሚያደርግ አመላክቷል፡፡

 

በአገራችን በጸረ-ተሕዋሲያን መድኃኒቶችን በጀርሞች መለመድ ችግር ምክንያት ምን ያህል ኪሳራ፣ ምን ያህል ሰዎች ለከፍተኛ ድህነት እንደሚዳረጉ፣ የኤክስፖርት መጠን በምን ያህል እንደሚቀንስ እና የእንስሳት ምርት በዓመት ምን ያህል እንደሚቀንስ ስፋትና ጥልቀት ያለው ጥናት ባለመካሄዱ በመረጃ አስደግፎ መናገር የሚያዳግት ነው የሚሉት በኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት መድኃኒት ጥራትና ደረጃ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰለሞን ከበደ ቢሆንም ካለን የእንስሳት ጤና ሥርዓት፣ የኑሮ ደረጃ እንዲሁም ለጸረ-ተሕዋሲያን መድኃኒቶች አያያዝ እና አጠቃቀም ካለን እውቀትና ግንዛቤ አንጻር ችግሩ የበለጠ ሊከፋ እንደሚችል በተበታተነ መልኩም ቢሆን በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምርምር ኢንስቲትዩቶች የሚወጡ የምርምር ውጤቶች እና በቅርብ ጊዜ በባለሥልጣኑ የእንስሳት ውጤቶች፣ መድኃኒትና መኖ ጥራት ምርመራ ማዕከል በተካሄዱት የዳሰሳ ጥናቶችም አመላካች መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም የችግሩ አሳሳቢነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ይህንን ችግር ለመቅረፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለም የጤና ድርጅት(WHO)፣ የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት(WOAH)፣ የዓለም ምግብና የእርሻ ድርጅት(FAO) እና የተባበሩት መንግሰታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም(UNEP) የጸረ-ተሕዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ለመከላከል የአምስት ዓመት ስትራተጂ እቅድ በመነደፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ስትራተጂ መሰረት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር(MOH)፣ የግብርና ሚኒስቴር(MOA) እና የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ(EPA) በአንድ ላይ በመሆን የጸረ-ሕህዋስያን መድኃኒቶች በጀርሞች መለመድ ለመከላከል የአምስት አመት ስትራተጂክ እቅድ ማዘጋጀቷን ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

 

ከስትራተጂክ እቅዱ በመነሳት በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት ዶ/ር ሰለሞን በዋናነት ከእንስሳት ሐኪሞች ማኅበር እና ከብሩክ ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ለስድስት የእንስሳት ዝርያዎች አስፈላጊ የሆኑ የእንስሳት መድኃኒቶች ዝርዝር (Essential veterinary drug list) ከተመረጡ ዩንቨርሲቲዎች ማለትም ለውሻና ድመት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ ለጋማ ከብቶች በባህር ዳር እና ወሎ ዩነቨርሲቲ፣ ለዶሮ በሐሮማያ ዩንቨርሲቲ፣ ለበግና ፍየል በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ ለዳልጋ ከብቶች በጅማ ዩነቨርሲቲ እና ለግመሎች በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ከተወጣጡ የእንስሳት ዝርያ መሰረት ተድረጎ በተዋቀረ ግብረ ኃይል መዘርዝሩ መዘጋጀቱን ያብራራሉ፡፡ የተዘጋጀው የስድስት እንስሳት ዝርያዎች አስፈላጊ የሆኑ የእንስሳት መድኃኒቶች መዘርዝር በተመረጡ ከ 3-5 በሙያው እና በዘርፉ የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች እንዲገመገም የተላከ ሲሆን በዚህ ወር መጨረሻ በመድረክ እንዲገመገም ተደርጎ በሚመለከተው አካል ፀድቆ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል፡፡

 

የመዘርዝሮቹ መዘጋጀት በእንስሳት ጤና አገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ገበያ ላይ መገኘት ያለባቸውን የእንስሳት መድኃኒቶች ጥቆማ የሚሰጥ ሲሆን መዘርዝሩን እና የእንስሳት ሕክምና አሰጣጥ መመሪያ(Standard Veterinary Treatment Guideline) መሰረት በማድረግ በፊልድ ላይ የሚሰሩ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች የሚፈልጓቸውን መድኃኒቶች በገበያ ላይ እንዲገኙ ጥያቄ ያቀርባሉ ተብሎ ይታመናል የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን ይሄንንም ጥያቄ መሰረት በማድረግ አቢሲኒያ የእንስሳት መድኃኒት አስመጪዎች እና ጅምላ አከፋፋዮች ማኅበር፣ የእንስሳት መድኃኒት አስመጪዎች እና አምራቾች የተጠየቁት መድኃኒቶች ሕጋዊ ሂደቱን ተከትለው ተመዝግበው ወደ ገበያ እንዲቀርቡ የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ እንደሚገመት ገልጸዋል፡፡

 

የእንስሳት መድሃኒት አቅረቦትንና ዋጋን ለማሻሻል እና በተጨማሪም በግል የእንስሳት መድሃኒት አስመጪ ባለሀብቶች የማያስመጧቸውን አስፈላጊ የእንስሳት መድሃኒቶች አቅርቦት ላማሻሻል ልክ እንደ በጤና ሚኒሰቴር የኢትዮጲያ የመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በግብረና ሚኒስቴር የመንግስት የልማት ድርጅት የሆነው የግብረና ግብዓት አቅርቦት ኮርፖሬሽን የእንስሳት መድሃኒት አስመጪ ይህን ክፍተት ቢሞላ የጸረ-ተሕዋስያንን በጀርሞች መለመድ በመከላከል በኩል የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ዶ/ር ሰለሞን አብራርተዋል፡፡

 

በአጠቃላይ የጸረ-ተሕዋሲያን መድኃኒት በጀርሞች መለመድን ችግር ለመቀልበስ የሚያስችል ስልት መንደፍ እና መተግበር፤ በእንስሳት ኃብት ልማት ዘርፍ ውስጥ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ማሳደግ እንዲሁም ከሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው የሚሉት ዶ/ር ሰለሞን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን መሰል የመድኃኒት አማራጮችን ለማስፋት እና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

 

ለበለጠ መረጃ፦

ስልክ፡- 011 553 45 20

ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et

ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/Ethiopian Agricultural Authority

ቴሌግራም፡- eaa_123

ነፃ ጥሪ፡- 8083

ፖ.ሳ.ቁ፡- 31303

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የሚሌ የእንስሳት ኳራንታይን ጣቢያን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችልየምክክር መድረክ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያዎችና ቼክ ፖስቶችን በመገንባትና በግንባታ ላይ ያሉትን ደረጃቸውን እንዲጠብቁና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ የውስጥ አደረጃጀታቸውን በመፈተሸ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ሞያዊ ድጋፍና ቁጥጥር በማድረግ በሌሎች አገራት ተቀባይነት እንዲኖራቸው እንዲሁም በተቀባይ ሀገሮች በማስገምገም እውቅና እንዲያገኙ የማድረግ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይሄን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለውን የሚሌ እንስሳት ኳራንታይን ጣቢያን ሥራ ለመጀመር የሚያስችል የምክክር መድረክ ከቁም እንስሳት ላኪዎች፣ ከቁም እንስሳት ላኪዎች ማሕበርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ አካሂዷል፡፡

 

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ አገራችን ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ኃብቷ ከአፍሪካ የቀዳሚነቱ ከዓለም ደግሞ ከመጀመሪያዎቹ 10 አገራት ተርታ የምትመደብ ቢሆንም ከዘርፉ ባላት ኃብት ልክ መጠቀም አልቻለችም ብለዋል፡፡ ከእኛ በብዙ እጥፍ ያነሰ የቁም እንስሳት ኃብት ቁጥር ያላቸው ጎረቤት አገራት እንኳ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው በመስራታቸውና አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እንዲሁም የግብይት ሥርዓታቸውን በማዘመን በስፋት ኤክስፖርት አድረገው የተሻለ ገቢ በማግኜት ላይ ይገኛሉ ያሉት አምባሳደር ድሪባ ከእንስሳት እርባታ እስከ ቁጥጥር ሥርዓታችን ድረስ መዋቅራዊ የሆኑ ማነቆዎች በመኖራቸውና በተለይም የግብይት ሥርዓቱ ሕግን ያልተከተለና ያልዘመነ መሆኑ አገራችን ከዘርፉ በሚገባት ልክ ተጠቃሚ እንዳትሆን ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

 

አምባሳደር ድሪባ አክለውም በእንስሳት ዘርፍ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋትና መተግበር ብሎም የንግድ ሥርዓቱን ማዘመንና በዓለምአቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት ከዘርፉ የሚገኜውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣንም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ዘርፉን ካሉበት ችግሮች ለማላቀቅና የአገራችንን ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ የሚያስችሉ የሕግ፣ የአሰራርና የመዋቅር ማሻሻያዎችን እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

 

የምክክር መድረኩ ዓላማም የቁም እንስሳት ላኪዎችን፣ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማሕበርና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን እና ኳራንቲን ጣቢውን ለማስተዳደር ውል የወሰደውን ድርጅት በማስተዋወቅ የሚሌ እንስሳት ኳራንቲን ጣቢያውን ሥራ ለማስጀመር ነው ያሉት አምባሳደር ድሪባ መንግስት የሚሌ ኳራንታይን ጣቢያ ሥራ መጀመር  እንስሳቶቻችን ከበሽታ ነጻ መሆናቸው እዚሁ አገራችን ላይ ተረጋግጦ እንዲላክ በማድረግ እንስሰታን በስፋት ወደ ውጭ ለመላክና አገልግሎቱን ለማሻሻል አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡ ደራጀውን የጠበቀ ኳራንቲን ራሱ ገንብቶ ራሱ አገልግሎት መሰጠት ውጤታማ ለመሆን አሰቸጋሪ ሰለሆነ የሌሎች አገራትን ተሞክሮና ልምድ በመውሰድ በመመሪያ መሰረት የሚሌ የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያን ሙሐመድ ሐሚድ አሊሳ ወደ ተባለ ግል ድርጅት ኢንዲዞር በማድረግ ሥራ ለማስጀመር በሥራ ላይ መሆኑን አምባሳደር ድሪባ ተናግረዋል፡፡

 

በምክክር መድረኩ ላይ በሚሌ እንስሳት ኳራንታይን ጣቢያው የግል ድርጅቱ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን፣ የቁም እንስሳት ላኪዎች፣ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማሕበርና  የሌሎች ባለድርሻ አካላት ተግባርና ኃላፊነት ምን ሊሆን ይገባል በሚለው ላይ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ሕገ-ወጥ የቁም እንስሳት ንግድ ለመከላከል፣ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ የሆኑ ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት እና አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ከማድረግ አኳያና ሌሎች በመንግስትና ኳራንቲን ጣቢያውን ለማስተዳደር ውል በወሰደው የግል ድርጅት በኩል በትኩረት ሊታዩ ይገባል ያሏቸውን ኃሳቦች ተሳታፊዎቹ አንስተዋል፡፡

 

የሚሌ የእንስሳት ኳራንቲን ጣቢያን ለማስተዳደር ውል የወሰደው ሙሐመድ ሐሚድ አሊሳ ድርጅትም አገልግሎቱን ለማዘመንና የቁም እንስሳት ንግዱን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተቀናጅቶ እንደሚሰራ ገልጧል፡፡

 

ባለሥልጣን መ/ቤቱ በውይይቱ ከባለድርሻ አካላት የተነሱትን ኃሳቦች ወስዶ ለዘርፉ እድገት በሚጠቅም መንገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ተባብሮ ያሰራል ያሉት የባለሥልጣን መ/ቤቱ የእንስሳት ሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሐሚድ ጀማል የቁም እንስሳትን በስፋት ኤክሰፖርት ለማድረግና የዘርፉን ተወዳዳሪነት ብሎም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚሌ እንስሳት ኳራንታይን ጣቢያ ሥራ መጀመር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ዶ/ር ሐሚድ አክለውም የሚሌ እንስሳት ኳራንታይን ጣቢያ ሥራ መጀመር የቁም እንስሳት ኤክስፖርተሮች ከአሁን ቀደም እንስሳቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ይደርስባቸው የነበረውን መንገላታትና አላስፈላጊ ወጭ በመቀነስ በኩል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በቀጣይም ደረጃቸውን የጠበቁ የኳራንቲን ጣቢያዎች እንዲገነቡ በማድረግና ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን በማሟላትና በማዘመን ከአሁን ቀደም ከነበሩን የቁም እንስሳት ኤክስፖርት መዳረሻ ገበያዎቻችን ማለትም ከመካከለኛ ምስራቅ እና ከሰሜን አፍርካ አገራት በተጨማሪ ለአውሮፓ እና ለሌሎች አገራት በመላክ የአገራችንን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

 

በመጨረሻም የሚሌ እንስሳት ኳራንቲን ጣቢያው የሚሰጠውን አገልግሎት ለመጠቀምና በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍና የቁም እንስሳትንን ንግድ ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ከስምምነት ላይ በመድረስ የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡

 

ለበለጠ መረጃ፦

ስልክ፡- 011 553 45 20

ዌብሳይት፡- www.eaa.gov.et

ፌስቡክ፡- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን/Ethiopian Agricultural Authority

ቴሌግራም፡- eaa_123

ነፃ ጥሪ፡- 8083

ፖ.ሳ.ቁ፡- 31303

 

 

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፤

«በአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ በመሥራት የባለሥልጣኑን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተን እየሰራን ነው!»

~ዶ/ር ዳንኤል ጌታቸው

በኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ ኃላፊ

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካከል በሚወጡና በሚገቡ የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና የመኖ ግብዓት ላይ የሰነድና አካላዊ ምርመራ ማድረግ ይገኝበታል፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬትም በባለሥልጣኔ የአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ በመገኜት የኬላውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ከኬላው ኃላፊ ዶ/ር ዳንኤል ጌታቸው ጋር ቆይታ አድርገን የነበር ሲሆን ጽሁፉን ለማኅበራዊ ሚዲያ ተከታቻችን በሚመች መልኩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ መልካም ንባብ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ የአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ ተግባርና ኃላፊነት ምንድን ነው?

ዶ/ር ዳንኤል፦ በአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ የሚከናወኑ ሥራዎች በዋነኛነት በሚወጡና በሚገቡ የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና የመኖ ግብዓት ላይ የሰነድ እና አካላዊ ጥልቅ ምርመራ(Inspection) የማድረግ ሥራ መሥራት ነው፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ኬላው የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ዳንኤል፦ የአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መድኃኒት እና ጥራቱና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መኖና የመኖ ግብዓት ለሕብረተሰቡ እንዲደርስ ማድረግ ነው:: ይህን ተከትሎ የሰነድ እና አካላዊ ጥልቅ ምርመራ ተደርጎባቸው የተረጋገጡ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና እንዲወጡ የመልቀቂያ ፈቃድ መስጠት ነው፡፡ ማለትም በአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡና ከአገር በሚወጡ ምርቶች ላይ በምርመራ ወቅት አጠራጣሪ ሆነው ሲገኙ ናሙና ወስዶ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ላቦራቶሪ መላክና በላቦራቶሪው ውጤት መሰረት መስፈርቱን ለሚያሟሉ የመልቀቂያ ፈቃድ በመስጠት፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ የሚወጡና የሚገቡ የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና የመኖ ግብዓት የምትቆጣጠሩበት አግባብ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ዳንኤል፦ የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና የመኖ ግብዓት የመግቢያና መውጫ ፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ 02/2009 ላይ መሰረት በማድረግ በሚወጡና በሚገቡ የእንስሳት መድኃኒትና መኖና የመኖ ግብዓት ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ተጠብቆ ለአገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ወደ ውጪ በሚላኩት ላይም በዚሁ አግባብ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ቁጥጥር በምታደርጉበት ወቅት የእንስሳት መድኃኒት ወይም መኖው ላይ ችግር እንዳለበት ካረጋገጣችሁ የምትወስዱት እርምጃ ምንድነው?

ዶ/ር ዳንኤል፦ የእንስሳት መደኃኒትም ሆነ መኖ የጥራት ችግር ሲያጋጥመው በመመሪያው መሰረት ውሳኔ እንወስናለን፤ ለምሳሌ የእንስሳት መድኃኒት ችግር እንዳለበት ጥርጣሬ ሲያድርብን ናሙና በመውሰድ ለላቦራቶሪ እንልክላን፡፡ ናሙናው በላቦራቶሪ ተመርምሮ ችግር ወይም የጥራት ጉድለት እንዳለበት ከተረጋገጠ መድኃኒቱ ለሕብረተሰቡ ሳይሰራጭ በባለስልጣኑ ውሳኔ መሰረት እንዲወገድ የሚደረግ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ ወደመጡበት አገር እንዲመለሱ እና እዚሁ እንዲወገዱ የተደረጉ መድኃኒቶችም አሉ፡፡ በመኖም በኩል የጥራት ችግር ተገኝቶበት በማቃጠል የተወገደ መኖም አለ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላችሁ ቅንጅታዊ አሰራር ምን ይመስላል?

ዶ/ር ዳንኤል፦ እንደሚታወቀው የቁጥጥር ሥራ ለአንድ ክፍል ወይም ለአንድ ተቋም የሚተው አይደለም፡፡ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ተሳትፎ የሚጠይቅ ሲሆን የአዳማ/ሞጆ መግቢያና መውጫ ኬላ በሚገቡና በሚወጡ የእንስሳት መድኃኒትና መኖዎች ላይ መስፈርቱን አሟልተው ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ እንዲደርሱ በሚያደርገው የቁጥጥር ሥራ በርካታ አካላት ይሳተፉበታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የምርመራ ላቦራቶሪዎች፣ ጉሙሩክ፣ ኢባትሎአድ፣ አስምጭና ላኪ ድርጅቶች፣ የጸጥታ አካላት እና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ይገኙበትል፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት የምታከናውኗቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ዳንኤል፦ እኛ የምንሰራው የቁጥጥር ሥራ በመሆኑና የቁጥጥር ሥራ ደግሞ በባሕሪው ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው፡፡ እኛም ይሄን በመረዳት አገልግሎታችን ከኪራይ ሰብሳቢነትና ከብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን የምናከናውን ሲሆን ለአብነትም በሚገቡና በሚወጡ የእንስሳት መድኃኒት፣ መኖና የመኖ ግብዓት አካላዊ ምርመራ ስናደርግ ሁለትና ከዚያ በላይ ባለሙያዎች እንዲሆኑና ሥራውን በቡድን እንዲሰሩ ማድረግ አንደኛው ነው፡፡ ማለትም አካላዊ ምርመራ ሲካሄድ በተለያዩ ባለሙያዎች የሚጣራና የሚፈተሸ በመሆኑ ችግሩን ይቀርፈዋል ብለን እናምናለን፡፡ በተጨማሪም የኪራይ ሰብሳቢነትና የብልሹ አሰራርን በተመለከተ ለባለሙያዎቻችን ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር እና ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የአሰራር ሥርዓቶችን በመተግበር ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እንሰራለን፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ የ2015 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀማችሁ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ዳንኤል፦ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በ2015 በጀት ዓመት በአዲስ አደረጃጀት ተዋቅሮ እየሰራ ሲሆን ኬላም ላይ የሚሰሩ ሥራዎች በአዲስ ቢሆንም ነገር ግን እቅዱ በአዲስ መልክ ተሰርቶ ከማዕከል ወደ እኛ ስላልወረደ ቀድሞ በነበረው እቅድ እየሰራን እንገኛለን፡፡ በዚህም 100% የሚወጡና የሚገቡ የእንስሳት መኖና የመኖ ግብዓት የሰነድና አካላዊ ጥልቅ ምርመራ ሥራዎችን እንሰራለን ብለን አቅደን በ1ኛው ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸማችን 100% ሲሆን በተመሳሳይ በቀጣይ ሩብ ዓመት የኮንሳይመንት ላቦራቶሪ ምርመራ በማካተት የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ በመሥራት የባለሥልጣኑን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ተቀናጅተንና ተናበን የምንሰራ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ተቋሙ እንደ አዲስ ከመደራጀቱ አንፃር ከላብራቶሪ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ቢኖርና ወጥ የሆነ የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት በላብራቶሪ የተደገፈ የኢንስፔክሽን ሥራ ቢሰራና ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት እና ጥራቱና ደኅንነቱ የተረጋገጠ መኖ ለሕብረተሰቡ በማቅረብ ባለስልጣኑ የተቋቋመበትን ዓላማና ተግባር በብቃት ለመወጣት መልካም ነው እላለሁ፡፡ሕዝብ ግንኙነት፦ በስራችሁ ላይ ቅሬታዎች ሲኖሩ የምታስተናግዱባቸውና የምትፈቱባቸው መንገዶች ካሉ ቢገልፁልን?ዶ/ር ዳንኤል፦ በሥራችን ላይ ቅሬታዎች ሲኖሩ ቅሬታ የምንቀበልበትና ቅሬታውን የምንፈታበት የአሰራር ሥርዓት ያለን ሲሆን የቀረበው ቅሬታ በኬላው አቅም የሚፈታ ከሆነ በኬላው፤ ከኬላው አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ ለባለሥልጣኑ የበላይ አካል በማቅረብ የሚፈታበት አግባብ አለ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ሥራችሁን ስታከናውኑ የገጠማችሁ ችግር ካለ?

ዶ/ር ዳንኤል፦ ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ አንዳንዴ ሠራተኛው አዲስ ሲሆን የኛን መልቀቂያ ፈቃድ ሳይጠይቅ መልቀቂያ የሚሰጠበት አግባቦች አጋጥመውናል፡፡ ቢሆንም ችገሩን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገናኘት መፍትኄ በመስጠት ችግሩ እንዳይደገም እየሠራን እንገኛለን፡፡ በተጨማሪም ከአንድ መስኮት አገልግሎት(ESW) ከመጠቀማችን ጋር ተያይዞ አስመጪው እቃው ወደብ ከመድረሱ ከወር/ከ15 ቀን በፊት ሰነድ የማስገባት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ይሄ ደግሞ እኛ ላይ የሥራ ጫና ከመፍጠሩም ባሻገር ለአሰራር ምቹ አይደለም፡፡ ስለሆነም አስመጪዎች ሰነድ ከማስገባታቸው በፊት እቃው መግባቱን አረጋግጠው ሰነድ ቢያስገቡና መመሪያውን ተከትለው ቢሰሩ መልካም ነው እላለሁ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?

ዶ/ር ዳንኤል፦ ጥራቱ፣ ደኅንነቱና ፈዋሽነቱ የተረጋገጠ የእንስሳት መድኃኒት እና ጥራቱና ደኅንነቱ የተጠበቀ የእንስሳት መኖና የመኖ ግብዓት ለማረጋገጥ ሁሉም በባለስልጣኑ የሚገኙ የሥራ ክፍሎች ከፈቃድ ሰጪ እስከ ላብራቶሪ ያሉት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጎልበትና በመናበብ መስራት አለባቸው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ችግሮች ስለሚያጋጥሙን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ መድኃኒት በሌላ ሽፋን ቢመጣ በፊት የተመዘገበበትን ሽፋን ስለማናውቅ ኬላ ላይ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከቅድመ ግዥ ፈቃድ ጀምሮ እስከ ላቦራቶሪ ድረስ ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ አንድ ላይ ቢሰራ ውጤታማ ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡ ላቦራቶሪዎችም እኛ የወሰድነውን መድኃኒት በአግባቡ መርምረው ውጤቱን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ቢያሳውቁን የተሻለ ሥራ መስራት ይቻላልና ደግሜ ደጋግሜ ቅንጅታዊ አሰራራችንን እናሳድግ እላለሁ፡፡

ሕዝብ ግንኙነት፦ ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰሀግናለሁ!

ዶ/ር ዳንኤል፦ እኔም አመሰግናለሁ

@የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የፌስቡክ ገጻችን ይቀላቀሉ፡- https://www.facebook.com/EthiopianAgriculturalAuthority

የቴሌግራም ገጻችንን ይቀላቀሉ፦ @eaa_123

ውይይት ተካሄደ

በእንስሳት ስጋና ተረፈ ስጋ ምርት የእሴት ሰንሰለት ተግዳሮቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄደ፤
*****
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በእንስሳት ሥጋ ኤክስፖርት ዕሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉትን ችግሮች በጋራ በመለየት፤ የጋራ መፍትሄና ዕቅድ በማስቀመጥና በመተግበር የሥጋና የተረፈ ምርቱን ኤክስፖርት በማሳደግ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካል ከሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄደ፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢፌዲሪ ግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ፍቅሩ ረጋሳ ሲሆኑ የውይይቱ ዋና ዓለማ በእንስሳት ስጋና ተረፈ ስጋ ምርት ጥራት ደህንነትና ጤና የእሴት ሰንሰለት ውስጥ እስከ ኤክስፖርት ድረስ ያለውን አቅምና ተግዳሮት ዘርፉ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ ለወደፊቱ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንዲቻል ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም የኤክስፖርት ቄራዎች ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ሹመት ባቀረቡት ገለፃ በ2014 በጀት ዓመት 22,689 ቶን ሥጋና ተረፈ ምርት በመላክ 119.14 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ እንደተገኘና ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 79.12 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር 40 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አጋጠሙ ካሏቸው ተግዳሮቶች መካከል የግብዓት አቅርቦት እጥረት (በብዛት፣ በጥራት፣ በሚፈለገዉ ጊዜ እና ዋጋ) ለዚህም የእንስሳት እርባታችን አለመዘመንና ገበያ ተኮር አለመሆን ትልቁን ድርሻ የያዘ እንደሆነ ጠቅሰው በህገ-ወጥ ንግድ (ኮንትሮባንድ) ወደ ውጪ ለሚወጡት እንስሳት የሚከፈል ዋጋ የተሻለ መሆንና የሀገር ውስጥ የእንስሳት የመግዣ ዋጋ ከፍተኛ መሆን፣ ከግዥ ጣቢያ እስከ ቄራ ድረስ በመሃል ያለ ደላላ ከፍተኛ ፤መሆን ደረጃውን የጠበቀ የእንስሳት ትራንስፖርት መስጫ ተሽከርካሪ እጥረት፣ በሎጂስትክ (ኮንቲኔር) እጥረት ምክንያት ለኤክስፖርት የተዘጋጁ ምርቶችን አለመላክ (በተለይ የሥጋ እርድ ተረፈ ምርት ኤክስፖርት)፣ እንዲሁም የመዳረሻ ገበያ ውስንነት መኖር ተጠቃሽ እንደሆኑ አብራርተዋል::
ለዚህም እንደመፍትሄ ብለው ካቀረቧቸው ውስጥ ከእንስሳት በሽታ ነፃ የሆነ ቀጠናን ለመመስረት ትኩረት መስጠት፤የእንስሳት ደህንነት፣ ጥበቃ፣ አያያዝ እና እንክብካቤ ስርዓት መዘርጋት፤የዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም መዘርጋትና መተግበር፤መሰረተ ልማት ያለዉ የእንስሳት ማቆያና የገበያ ማዕከላትን መገንባት፤ የእንስሳት ልየታና ምዝገባ ሥርዓት መዘርጋት(Traceability፤ ዘመናዊ የእንስሳት ማጓጓዣ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ማመቻቸት፤የእንስሳት ኮትሮባንድ ንግድ መቆጣጠር እና በሂደቱም የሚያዙትን እንስሳት ለኤክስፖርት ቄራዎች የሚቀርቡበትን ስርዓት መዘርጋት እና በመደበኛ እና በጥቁር ገበያ መካካል ያለዉን የዉጪ ምንዛሪ ገበያ ዋጋ ማቀራረብ፤ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ቤቱ በቀረበው ገለፃ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ በቀረቡ ችግሮችና መፍትሄዎች እንዲሁም በቀጣይ ሊከሰቱ በሚችሉ ስጋቶች ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ በቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚመለከተውን የስራ ድርሻ በመውሰድ የእቅዳቸው አካል አድርደው መስራት እንደሚገባና ይህም ፕሮግራም ወጥቶለት በየጊዜው እየተገመገመ መሄድ እንዳለበት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡

May be an image of 1 person and text

Languages
Scroll to Top